top of page

የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄ የቀረበበት የዶ/ር መረራ አቤቱታ ለመጪው ዓመት ተቀጠረ


Photo: Reporter Ethiopia

የፀረ ሽብርተኝነት አዋጁን በመጥቀስ ዓቃቤ ሕግ ምስክሮችንና ማስረጃዎችን መከልከሉን የተቃወሙት መረራ ጉዲና (ዶ/ር)፣ ጉዳያቸው የሕገ መንግሥት ትርጉም ስለሚያስፈልገው የአጣሪ ጉባዔውን ውሳኔ እንዲጠjቁ ተነገራቸው፡፡ ውሳኔውን የሚሰሙት በሚቀጥለው ዓመት ነው፡፡

ሦስት የተለያዩ የወንጀል ክሶች የተመሠረቱባቸው ዶ/ር መረራ በክሶቹ የተጠቀሱባቸው የሕግ አንቀጾች የምስክሮችና የማስረጃ ዝርዝሮች እንዳይደርሳቸው የማይከለክሉ መሆኑን በመግለጽ፣ ከሳሽ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/01 አንቀጽ 32ን በመጥቀስ እንዳይሰጣቸው መከልከሉን ተቃውመው ነበር፡፡

ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32(1)ሀ፣ ለ፣ 38(1)፣ 27(1)፣ 238(1) እና (2)ን አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 12(1)፣ 2(1) የወንጀል ሕግ 486(ለ) ማለትም በጋራ በመተባበር፣ ወንጀል ለማድረግ በማደም፣ በሕገ መንግሥቱ ላይ ወንጀል ለማድረግ በመስማማት፣ የሐሰት ወሬ በማውራትና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የመጣስ ወንጀል ክስ ተመሥርቶባቸው ሳለ፣ የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 32 በመጥቀስ የምስክሮች ዝርዝር እንዳይሰጣቸው መከልከሉ ተገቢ ያልሆነና ሕገ መንግሥቱን የሚጥስ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የቀረበለትን የመቃወሚያ አቤቱታ የመረመረው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት፣ ‹‹የሕገ መንግሥት ትርጉም ያስፈልገዋል ወይስ አያስፈልገውም?›› በማለት ጉዳዩን ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት አጣሪ ጉባዔ የላከው ቢሆንም፣ ውሳኔው ሊደርስ ባለመቻሉ ለቀጣይ ዓመት ጥቅምት 6 ቀን 2009 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

የምስክሮች ዝርዝር ‹‹ለተከሳሽ ሊሰጥ ይገባል ወይስ አይገባም?›› የሚሉ ጥያቄዎች የተነሱት በዶ/ር መረራ ክስ ብቻ አለመሆኑን የጠቆመው ፍርድ ቤቱ፣ በርካታ የክስ መዝገቦች ላይ ጉዳዩ በመነሳቱ ቀደም ብሎ የሕገ መንግሥት ትርጉም ያስፈልገዋል ወይስ አያስፈልገውም የሚለውን ምክር ቤቱ ውሳኔ እንዲሰጥበት ትዕዛዝ መስጠቱን አስታውሷል፡፡ ምክር ቤቱ ግን ለሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ መላኩን ከመግለጽ ውጪ ያለው ነገር ስለሌለ ውሳኔውን መጠበቅ የግድ እንደሚል አስረድቷል፡፡

የዶ/ር መረራ ጠበቆች ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዱት፣ ዶ/ር መረራ ከታሰሩ ዘጠኝ ወራት ሞልተዋቸዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ደግሞ የዓመቱን ሥራ ሊያጠናቅቅ የቀረው ከ15 ቀናት አይበልጥም፡፡ በመሆኑም ፍርድ ቤቱ በራሱ የመተርጎም ሥልጣን ስላለው ተርጉሞ ወይም የምክር ቤቱ ውሳኔ የሚፈጥንበት ሁኔታ ካለ ተባብሯቸው፣ ወደሚቀጥለው ዓመት ከመተላለፉ በፊት ውሳኔ እንዲሰጣቸው ጠይቀው ነበር፡፡

ፍርድ ቤቱ በሰጠው ምላሽ ዶ/ር መረራ በክርክር መቃወሚያቸው ምክንያት ጉዳዩ ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ለትርጉም መላኩን አስታውሶ፣ የመቃወሚያ ሐሳባቸውን ለማንሳት ፈልገው ከሆነ ጥያቄ አቅርቦላቸዋል፡፡ የዶ/ር መረራ ጠበቆች ተመካክረው ምላሽ ሲሰጡ መቃወሚያ ያቀረቡት ሕጉ በሚፈቅድላቸው መሆኑን በመጠቆምና ፍርድ ቤቱም ትዕዛዝ እንደሰጠበት ተናግረው፣ መቃወሚያቸውን እንደማያነሱ ገልጸዋል፡፡

በመቀጠልም ዶ/ር መረራ የእምነት ክህደት ቃላቸውን እንኳን ሳይሰጡ እየተጉላሉ መሆኑን ገልጸው፣ ጉዳዩ በአጭር ቀናት ውስጥ እንዲታይላቸው ጠይቀዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ መቃወሚያችሁን አንሱ የሚል ጥያቄ አለማቅረቡን ገልጾ፣ እሳቸው በራሳቸው ተነሳሽነት መቃወሚያቸውን እያነሱ ስለመሆናቸው ለማወቅ መሆኑን አስታውቋል፡፡

ፍርድ ቤቱ ዶ/ር መረራም ሆኑ ሌላ ተከሳሽ እንዲመላለስና እንዲጉላላ ፍላጎት እንደሌለው በመንገር፣ መዝገቦችን የሚያስተናግደው ክስ በተመሠረተበት ጊዜ (ዕድሜ) ቅደም ተከተል ከመሆኑ አንፃር የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ውሳኔ መጠበቁ ለተከሳሹም ሆነ ለፍርድ ቤቱ ጥቅም ስላለው፣ ለጥቅምት 6 ቀን 2009 ዓ.ም. መሸጋገሩ የግድ መሆኑን በማስረዳት ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

የዶ/ር መረራ ጠበቃ ዶ/ር ያዕቆብ ኃይለ ማርያም፣ የጥብቅና ፈቃድና ውክልና እያላቸው ማረሚያ ቤት ደንበኛቸውን እንዳይጎበኙና እንዳያነጋግሩ እንደከለከላቸው ላቀረቡት ጥያቄ፣ ማረሚያ ቤቱ እንዲያገናኛቸው ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

 

Copyrights Disclaimer: BOLEPOST.COM is a video and news aggregator; thus, we claim no ownership of copyrighted videos and audios posted here on our website or shared via our social media pages. Videos, audios, images and other published materials on our website and social media pages must be treated as such.


bottom of page