top of page

Reporter Ethiopia - የአቶ አባዱላ መልቀቂያ በኢሕአዴግ ተቀባይነት አገኘ


አቶ አባዱላ ገመዳ መልቀቂያቸው ተቀባይነት በማግኘቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔነታቸውን ያስረክባሉ

Reporter Ethiopia : የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ በመሆን ሲያገለግሉ የነበሩት አቶ አባዱላ ገመዳ፣ ከአፈ ጉባዔነት ለመልቀቅ ያቀረቡት ጥያቄ በኢሕአዴግ ተቀባይነት ማግኘቱ ታወቀ፡፡

በመስከረም ወር 2010 ዓ.ም. የመልቀቂያ ጥያቄያቸውን ለኢሕአዴግ ሊቀመንበር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝና ለኦሕዴድ ያቀረቡት አቶ አባዱላ ገመዳ፣ የጥያቄያቸውን ምላሽ እስካለፈው ሳምንት ድረስ ሲጠባበቁ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡

ባለፈው ሳምንት ግን የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የተቀበለው መሆኑን ምንጮች ገልጸዋል፡፡

ኦሕዴድ የአፈ ጉባዔውን የመልቀቂያ ጥያቄ እንደተቀበለው፣ የፓርቲው አባልና የኦሮሚያ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊም ለሪፖርተር አረጋግጠዋል፡፡

የኦሮሞ ሕዝብና የኦሕዴድ ክብር በመነካቱ ምክንያት ከአፈ ጉባዔነታቸው ለመልቀቅ መወሰናቸውን አቶ አባዱላ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ጉዳዩን አስመልክቶ ከአንድ ወር በፊት ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ፣ አቶ አባዱላ ኢሕአዴግ ለሚገዛበት ማዕከላዊ ዴሞክራሲያዊነት ስለሚገዙ በአፈ ጉባዔነታቸው ይቀጥላሉ ብለው እንደሚገምቱ ተናግረው እንደነበር መዘገባችን አይዘነጋም፡፡

የ59 ዓመቱ አቶ አባዱላ ቀደም ሲል በአገር መከላከያ ሚኒስቴር በሜጄር ጄኔራልነት ማዕረግ በተለያዩ ኃላፊነቶች ያገለገሉ ሲሆን፣ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንትም ነበሩ፡፡ ከ2003 ዓ.ም. ጀምሮ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ በመሆን በሥራ ላይ ቆይተዋል፡፡

(C) Reporter Ethiopia

bottom of page