top of page

‹‹በሕዝብና በመንግሥት መካከል ጥርጣሬና ግጭት እንዲፈጠር እያደረጉ ያሉ አካላት ለሕግ ይቀርባሉ››


Photo: Reporter

የኦሮሚያ ክልል መንግሥት

ሪፓርተር (Sept 27, 2017) - የኦሮሚያ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ሰኞ መስከረም 15 ቀን 2010 ዓ.ም. በወጣው መግለጫ፣ በክልሉ ሐሰተኛ መረጃዎችን በማሠራጨት በሕዝቦችና በመንግሥት መካከል ጥርጣሬና ግጭት እንዲፈጠር እያደረጉ ያሉ አካላት ለሕግ እንደሚቀርቡ አስታወቀ፡፡

የክልሉን የተሃድሶ አመራር ጠብ አጫሪና የአገር አንድነት ሥጋት አስመስሎ የማቅረብ አባዜ እንዳለና የክልሉን ሚዲያ፣ መሪ ድርጅትና አመራሩን በፕሮፓጋንዳ ዘመቻ በማዳከም ለኪራይ ሰብሳቢ ኃይሎች የተመቸና ደካማ ክልል እንዲኖር የማድረግ ፍላጎት ያለው አካል እንዳለ ቢሮው በመግለጫው አመልክቷል፡፡

የኦሮሚያ ክልል የጥልቅ ተሃድሶ እንቅስቃሴው ከተጀመረ ወዲህ የክልሉን ሕዝብ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ጠንካራ ዕርምጃዎችን እየወሰደ እንደሆነ የጠቆመው መግለጫው፣ የክልሉን ሕዝብ ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሲባል በክልሉ ሲስተዋሉ የነበሩ ሕገወጥ የመሬት ዘረፋ፣ የኮንትሮባንድ ንግድ፣ ሕገወጥ የዶላር ዝውውር፣ ሕገወጥ የማዕድን ዘረፋና በመሳሰሉት የኪራይ ሰብሳቢነት ተግባራት ላይ ጥብቅ ዕርምጃ በመውሰድና ለሕዝብ ጥቅም እንዲውሉ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ገልጿል፡፡

ሆኖም ያላግባብ ጥቅም ሲያግበሰብሱ የነበሩ ግለሰቦች የኪራይ ሰብሳቢነት ትግሉን ለማደናቀፍ የቻሉትን ሁሉ በማድረግ ላይ እንደሚገኙ አስታውቋል፡፡ ትግሉ መስዋዕትነት ያስከፈለና እያስከፈለ ቢሆንም፣ የሕዝብን ጥቅም እስካረጋገጠ ድረስ በማይቀለበስ ደረጃ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም ቢሮው በመግለጫው አስረድቷል፡፡

በኪራይ ሰብሳቢ አካላት ላይ እየተወሰደ ያለው ዕርምጃም የክልሉን ሕዝብ የማስደሰቱን ያህል፣ ጥቅማቸው የተነካባቸውን ግለሰቦችን እንዳስደነገጠ ጠቁሟል፡፡ ጥቅማቸው የተነካባቸው ግለሰቦች ያለ የሌለ ኃይላቸውን አሰባስበው የክልሉን አመራር፣ ከዚያም አልፎ የክልሉን ሕዝብና መንግሥት ስም ጥላሸት ለመቀባት ዘመቻ መክፈታቸውንም ገልጿል፡፡

በፕሮፓጋንዳ ዘመቻቸውም በክልሉ መንግሥት የፀረ ኪራይ ሰብሳቢነት ትግል ዕርምጃ ከተወሰደባቸው ኃይሎች ጋር የጥቅም ትስስር ያላቸውን ‹‹ብሎገሮች››፣ ‹‹አክቲቪስቶች››፣ ‹‹ጋዜጠኞች›› እንዲሁም የሐሰት ወሬዎችን በመፈብረክ የክልሉን መንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በፋሽስትነት የመፈረጅ፣ በክልሉ ሰው ሳይፈናቀል ተፈናቅሏል፣ ግጭት ሳይፈጠር ኦሮሞና እከሌ የሚባል ብሔረሰብ ተጋጭቷል በማለት አፍራሽ ፕሮፓጋንዳ እያሠራጩ እንደሚገኙም ቢሮው በመግለጫው አስረድቷል፡፡

‹‹እነዚህ እየተቀነባበሩ የሚሠራጩ የተንኮልና የሐሰት መረጃዎች ግብ የኦሮሞ ሕዝብና የክልሉ መንግሥት በአጎራባች ክልሎችና በክልሉ በሚኖሩ ብሔር ብሔረሰቦች ዘንድ በጥርጣሬ እንዲታዩ የማድረግ እኩይ ዓላማ ያለው እንደሆነ ግልጽ ነው፤›› ብሏል መግለጫው፡፡

ከዚህም በተጨማሪ የኪራይ ሰብሳቢነትን የጥቅም ገመድ በመበጣጠስ ላይ ያለውን የክልሉን የተሃድሶ አመራር ‹‹ጠብ አጫሪ›› እና ‹‹የአገር አንድነት ሥጋት›› አስመስሎ በማቅረብና የክልሉን ሚዲያ በማዳከም፣ ለኪራይ ሰብሳቢ ኃይሎች ደካማ ክልል የማድረግ ፍላጎት ያለው ኃይል መሆኑን ለክልሉና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ማስገንዘብ እንደሚወድ በመግለጫው አመልክቷል፡፡

የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት፣ የክልሉ ሕዝብና መንግሥት ተረጋግቶ የልማትና የፀረ ኪራይ ሰብሳቢነት ትግሉ እንዳይፋፍም እየተደረጉ ያሉ የተንኮልና የሐሰት ፕሮፓጋንዳዎችና በዚህ እኩይ ተግባር እየተሳተፉ ያሉ ግለሰቦችና ተቋማት እየተጋለጡ እንደሚሄዱ ግልጽ አድርጓል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የተፈጠረውን ችግር ለማረጋጋት ከሰጡት አቅጣጫ በተቃራኒ፣ የሐሰት መረጃዎችን በማሠራጨት በመንግሥትና በሕዝቦች መካከል ጥርጣሬና ግጭት እንዲፈጠር እያደረጉ ያሉ አካላትን የክልሉ መንግሥት ለሕግ እንዲቀርቡ እንደሚያደርግ መግለጫው አስታውቋል፡፡

(C) Reporter Ethiopia

bottom of page